×
Browse Products About Us Login / Sign Up Contact Us አማርኛ
African Law Archive
Logo
የፍርድ ቤት ውሳኔ 14184

      Sorry, pritning is not allowed

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ / ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት
የመ / ቁ 14184
ዳኞች፡- አቶ መንበረፀሐይ ታደሰ
አቶ ፍሥሐ ወርቅነህ
አቶ አብዱልቃድር መሐመድ
አቶ መስፍን ዕቁበዮናስ
ወ / ት ሂሩት መለሰ
አመልካች፡- አቶ ውርጌሳ ታደሠ
መልስ ሰጪ፡- አቶ መለሰ ተካ
አቶ ፍሬሰንበት አዝማች
አቶ በቀለ ዴልኬራ
አቶ አለሙ ደልሊቦ
አቶ ከተማ ኢብሣ
አቶ ወ /
ሰማያት ዲማ
አቶ ፍቃዱ ራህመቶ
አቶ አማረ ተሰማ
አቶ ኤፌሶን መጋቢ
በከሣሽነት ወይም በተከሣሽነት በሙግት ተካፋይ ስለመሆን - ስለ ባለጉዳዩ / ከሳሽ ወደ ፍርድ
ቤት ሳይቀርብ መቅረት - የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥሮች 73
አመልካች ጉዳዩ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት በችሎተ ባለመገናኘታቸው
ምክንያት ያቀረቡትን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ / ቤት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ
ቁጥር 73 መሰረት በመዝጋቱ እና ይህንኑ ትዕዛዝ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ / ቤት ጉዳዩ
በይግባኝ ቀርቦለት በአብላጫ ድምፅ በማጽናቱ የቀረበ አቤቱታ
ው ሳ ኔ፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍ / ቤትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍ /
ቤት የሰጣቸው ትዕዛዞች
ተሽረዋል ፡፡
1- ክስ ያቀረበ ሰው ክሱ የሚዘጋበት ክርክሩን እንዲሰማ ቀጠሮ በተያዘበት ቀን
ያልቀረበ እንደሆነ ነው ፡፡
2- ከተከሣሹ መልስ ለመቀበል የሚያዝ ቀጠሮ ተከሣሹ የጽሑፍ መልሱን ለማቅረብ
እንዲችል የሚያዝ ቀጠሮ እንጂ ሕጉ እንደሚያዘው ጉዳዩ የሚሰማበት ቀጠሮ
አይደለም ::
3- መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሳሽ ባይቀርብ ፍ / ቤቱ የተከሳሹን መልስ
ተቀብሎ ጉዳዩን ለተከታዩ ክንውን ማዘጋጀት እንጅ ክሱን መዝጋት የለበትም ፡፡
ሐምሌ 29 ቀን 1997 ዓ.ም የመ.ቁ 14184
ዳኞች መንበረፀሐይ ታደሰ
ፍሥሐ ወርቅነህ አብዱልቃድር መሃመድ መስፍን ዕቁበዮናስ ሂሩት መለሰ
አመልካች
መልስ ሰጪ
አቶ ወርጌሣ ታደሰ ጠበቃ ሀይሉ አግዘው
» መለሰ ተካ አቶ ፍሬሰንበት አዝማች » በቀለ ደልኬራ » አለሙ ደልዲቦ » ከተማ ኢብሣ » ወ / ሰማያት ዲማ ፍቃዱ ራህመቶ » አማረ ተሰማ
» ኤፌሶን መጋቢ
ሁሉም አልቀረቡም
በዚህ መዝገብ የቀረበው የህግ ነጥብ አንድ ጉዳይ በይግባኝ ፍ / ቤት በሚታይበት ወቅት ከተከራካሪዎቹ የአንዱ መቅረት የሚያስከትለው በሕጉ የተደነገገ ውጤት ምንድነው ? የሚል ነው :: ለዚሁ የሕግ ነጥብ መነሣት ምክንያት የሆነው ከፍተኛ ፍ / ቤት የአሁን አመልካቾች ጉዳዩ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ዕለት በችሎት ባለመገኘታቸው ምክንያት አመልካቾችን በሚመለከት ቀርቦ የነበረውን ይግባኝ በፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁ .73 መሠረት በመዝጋቱ ነው :: አመልካች መዝገቡ መልሶ እንዲከፈት ጥያቄ ቢያቀርብም ለባለጉዳዩ መቅረትም ሆነ ለጠበቃው መቅረት የቀረበው ምክንያት በቂ ስላልሆነ የተዘጋው ይግባኝ አይከፈትም በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል ፣ ጉዳዩ በይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ /
ቤትም የቀረበ ቢሆንም የከፍተኛ ፍ / ቤት የሰጠው ትዕዛዝ በድምጽ ብልጫ ፀንቷል ፡፡
በአመልካች ጠበቃ የሰበር አቤቱታ በመቅረቡና ጉዳዩ ያስቀርባል በመባሉ መልስ ሰጪ እንዲቀርቡ ታዞ በጉዳዩ መልስ ቀርቦአል :: የመልስ መልስም እንደዚሁ ቀርቦ ከማኀደሩ ጋር ተያይዞአል ::
የሰበር ችሎት በዚሁ በቀረበው የሰበር ማመልከቻ መነሻነት መታየት ያለበት ትልቁ የሕግ ትርጉም አንድ ፍርድ ቤት በይግባኝ ደረጃ ይግባኝ ባይ አልቀረበም በማለት
የይግባኝ መዘገቡን ለመዝጋት የሚችለው መቼ ነው ? የሚለው ሆኖ አግኝተነዋል ፡፡ የፍትሐብሄር የሙግት ሂደት የሚመራው በፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ነው :: በመሆኑም ማንኛውም በሙግት ሂደት የሚነሣ ጥያቄ መመለስ የሚኖርበት ሕጉ በሚያስቀምጠው ሥርዓት መሠረት ብቻ መሆን ይገባዋል ፡፡ የአንዱ ወይም የሌላው ተከራካሪ ፍርድ ቤት በያዘው ቀነ ቀጠሮ አለመገኘት የሚያስከትለው ውጤት ምንድነው ? የሚለው ነጥብም መሠረታዊ ከሆነው ከመክሰስ መብትና ክስን ከመከላከል መብት ጋር እጅጉን የተያያዘ በመሆኑ መስተናገድ የሚኖርበት ሕጉ በሚያስቀምጠው መስፈርት መሠረት ብቻ መሆን ይኖርበታል ::
የከፍተኛው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በከፊል ወድቅ ያደረገው የፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕጉን ቁጥር 73 በመጥቀስ ስለሆነ የትዕዛዙን ትክክል መሆን አለመሆን ለመመርመር በዚህ ቁጥር የሰፈረው ድንጋጌ ስለተከራካሪዎች መቅረብና አለመቅረብ የሚደነግጉትን ተዛማጅ ቁጥሮች መመልከት ያስፈልጋል ፣ በቁጥር 73 የሰፈረው ድንጋጌ
ባንድ ነገር ክስ ያቀረበ ሰው ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነና ተከሣሹ ቀርቦ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ከሣሹ በሌለበትም ቢሆን ፍርድ ቤቱ ተከሣሹ በሙሉ ወይም በከፊል ላመነው ጉዳይ የፍርድ ውሣኔ ለመስጠት ይችላል ፡፡ ከሣሹ የካደ እንደሆነ ግን
መዝገቡን በመዝጋት ያሰናብተዋል :: በማለት ይደነግጋል ፡፡ ከዚሁ ድንጋጌ ይዘት ለመገንዘብ እንደሚቻለው ክስ ያቀረበ ሰው ክሱ የሚዘጋበት የተከሣሽን መልስ ለመቀበል ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ በያዘበት ቀን ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ሳይሆን ክርክሩ እንዲሰማ ቀጠሮ በተያዘበት ቀነ ቀጠሮ ያልቀረቡ እንደሆነ ነው :: ከላይ እንደተገለፀው በመሠረቱ ማንም ሰው ክስ አቅርቦ ፍርድ ወይም ውሣኔ ማግኘት መብቱ ነው :: ይህን መብቱን ሊያጣ ወይም በከፊል ሊቀርበት የሚገባው ሕግ በግልጽ ለይቶ ባሰፈረው ምክንያት ብቻ ነው :: አንድን ጉዳይ ለማየት የተሰየመ ፍ / ቤት የተለያዩ ክንዋኔዎችን ለመፈፀም በርካታ ቀጠሮዎች እንደሚሰጥ የታወቀ ነው :: ክስ ያቀረበ ሰው በሁሉም ቀጠሮዎች እንዲገኝ የሚጠበቅበት ቢሆንም በተያዘው ቀጠሮ ባለመገኘቱ ምክንያት ያቀረበው ክስ ሊዘጋበት የሚችለው ግን ሕጉ ለይቶና ዘርዝሮ ባስቀመጣቸው ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ብቻ ነው ፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በቅጡ ለመገንዘብ የፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የከሣሽና / ወይም የተከሣሽ አለመቅረብ ( non appearance of parties ) አስመልክቶ ያስቀመጠውን ሥርዓት ከአጠቃላይ የሙግት ሂደት ጋር አገናዝቦ መመልከቱ ጠቃሚ ነው ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው በዚህ መዝገብ የሕግ ትርጉም የሚሻው ትልቁ ጥያቄ አንድ ከሣሽ ወይም ይግባኝ ባይ በቀነ ቀጠሮ አልቀረብክም ተብሎ ክሱ / ይግባኙ የሚዘጋበት
መቼ ነው ? የሚለው ነው :: ከሕጉ ቁጥሮች 69፣70፣73 ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሕጉ በተከራካሪ ወገኖች አለመቅረብ ምክንያት አንድ መዝገብ እንዲዘጋ ወይም ተከሣሹ በሌለበት የነገሩ መሰማት እንዲቀጥል ትዕዛዝ የሚሰጠው ከሣሽ ወይም ተከሣሹ ወይም ሁለቱም ጉዳዩ እንዲሰማ በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርቡ የቀረ እንደሆነ ነው :: ከጉዳዩ ጋር አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች የሚሉትን በቅደም ተከተል እንመልከት ::
69 ( 1 ) ነገሩን ለማየት ፍርድ ቤቱ በወሰነው ቀነ ቀጠሮ ከሣሽ ተከሣሾች ራሳቸው ወይም
ወኪሎቻቸው ተሟልተው መቅረብ አለባቸው :: የተከራካሪዎች ወገኖች መቅረብ
እንደተረጋገጠም ክርክሩ መሰማት ይጀምራል :: ተከሣሽ ያለመቅረብ
ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ከሣሽ ቀርቦ ተከሣሹ ያልቀረበ እንደሆነ ለጉዳዩ ውሣኔ የሚሰጠው ከዚህ ቀጥሎ በተመለከተው ሥርዓት ነው :: ( ሀ ) ለተከሣሹ የተላከለት መጥሪያ የደረሰው መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ በሌለበት
የነገሩ መሰማት ይቀጥላል :: ባንድ ነገር ክስ ያቀረበ ሰው ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ
የቀረ እንደሆነና ተከሣሹ ቀርቦ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ከሣሹ በሌለበትም ቢሆን ፍርድ ቤቱ ተከሣሹ በሙሉ ወይም በከፊል ላመነው ጉዳይ የፍርድ ውሣኔ ለመስጠት ይችላል ፡፡ ተከሣሹ የካደ እንደሆነ ግን መዝገቡን በመዝጋት ያሰናብተዋል ፡፡
አንድን ጉዳይ አይቶ ውሣኔ ለመወሰን በርካታ ቀጠሮዎችን ፍርድ ቤት እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህ በርካታ ቀጠሮዎች መካከል በአንዱ ወይም በሌላኛው ወይም በሁለቱም አለመቅረብ ምክንያት ፍርድ ቤት ከላይ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሠረት ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችለው የባለጉዳዮቹ መቅረት የተከሰተው ለመሰማት በተቀጠረበት ቀን እንደሆነ ብቻ ነው :: ስለዚህ ጉዳዩ ለመስማት ቀጠሮ የተያዘበትን ቀን ከሌሎች ቀጠሮዎች በተለየ ሁኔታ እንዲታዩ ህግ አውጪው መፈለጉ ግልጽ ነው :: በተለምዶ ብዙ ፍርድ ቤቶች መልስ ለመቀበል ከሣሽ ወይም ተከሣሽ ወይም ሁለቱም ያልቀረቡ እንደሆነ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ድንጋጌዎች በመጥቀስ ጉዳዩ እንዲዘጋ ወይም ተከሣሹ በሌለበት እንዲሰማ ትዕዛዝ የሚሰጡ ቢሆንም የድንጋጌዎቹ ይዘት ይህን አሠራር የሚደግፍ አይደለም :: መልስ ለመቀበል የሚያዝ ቀጠሮ ተከሣሹ የጽሁፍ መልሱን ለማቅረብ እንዲችል የሚያዝ ቀጠሮ እንጂ ሕጉ እንደሚያዘው ጉዳዩ የሚሰማበት ቀነ ቀጠሮ አይደለም በመሆኑም መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ሳይቀርብ ቢቀር ጉዳዩ ለመሰማት በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርብ ቀረ ተብሎ መዝገቡ ሊዘጋበት የሚችልበት የሕግ መሠረት የለም :: በመሠረቱ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ
የሚያዘው በአንድ ጉዳይ ክስ የተመሠረተበት ሰው በጉዳዩ ላይ የቀረበበትን ክስ ያምን ወይም ይክድ እንደሆነ ሃሣቡን በጽሁፍ እንዲያቀርብ ማስረጃም ካለው የማስረጃውን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ለማድረግ ነው ፡፡ በመሆኑም ከከሣሹ የሚጠበቅ ክንዋኔ የለም :: ከሣሹ ሳይቀርብ ቀረ እንኳን ቢባል በፍርድ ቤቱ የሥራ ሂደት ላይ የሚያስከትለው መስተጓጎል ሊኖር አይችልም :: በመሆኑም መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ባይቀርብ የተከሣሹን መልስ ተቀብሎ ለተከታዩ ክንውን ጉዳዩን ከማዘጋጀት አልፎ መዝገቡ ለመዝጋት በቂ ምክንያት የለም ፣ የመዝገብ መዘጋትን ያህል ትልቅ እርምጃ በአንድ ተከሣሽ ላይ ለመፈፀም ቢያንስ ከከሣሹ በኩል መፈፀም የነበረበት ነገር ግን ሳይፈፀም የቀረ በህግ የተደገፈ በቂ ምክንያት መኖር አለበት :: የተከሣሽን የጽሁፍ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሽ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ መዝገቡ እንደሚዘጋ የሚገልጽ ድንጋጌ በሥነ ሥርዓት ህጋችን የትኛውም ክፍል አይገኝም :: የህግ ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ የአንድን ተከሣሽ ክስ መዝጋት ደግሞ አግባብ አይሆንም ፡፡ ተከሣሹ ባለመቅረቡ ምክንያት ክሱ እንዲዘጋ ህጉ የሚያዘው ጉዳዩ እንዲሰማ ቀጠሮ በተያዘበት ዕለት ከሣሹ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ነው :: ከሕጉ አደረጃጀትም መገንዘብ እንደሚቻለው ክሱ የሚሰማው የክስና የመከላከያ ጽሁፎች ( ከ222-240 የፍትሀብሄር
ሥነሥርዓት ድንጋጌዎች መሠረት ) ልውውጥ ከተከናወነ በኋላ ነው ፡፡ የጽሁፉን ልውውጥ የሚመለከተው የሕጉ ክፍል ስለክስና ስለመከላከያ ጽሁፍ » በሚል ርዕስ ራሱን የቻለ አንድ ክፍል ሲሆን ከዚህ የጽሁፍ ልውውጥ በኋላ የሚከተለው ክንውን ክስን ስለመስማት ” በሚል ርዕስ ራሱን በቻለ ሌላ ምዕራፍ የምናገኘው ነው :: ( 241-273 ) ከዚህ የህጉ አደረጃጀት የጽሁፍ መልስ የሚቀርብበት ቀነ ቀጠሮ በመርህ ደረጃ የክሱ መሰማት ከሚከናወንበት ቀነ ቀጠሮ የተለየ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም :: ከህጉ አደረጃጀት ባሻገር የክስ መሰማትን የሚመለከተው የሙግት ሂደት በሁለት የተከፈለ ሲሆን ሁለቱም የከሣሽና የተከሣሽን መገኘት የሚጠይቅ ነገር ነው :: የመጀመሪያ ክስ ሲከፈት የሚፈፀመውን ሥነ ሥርዓት ( First hearing ) ለአብነት መመልከት ይቻላል ፡፡ በፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 24 ( 1 ) መሠረት ክሱ መሰማት በሚጀምርበት ቀን ፍርድ ቤቱ የባለጉዳዩቹን ማንነት ካረጋገጠ በኋላ ክሱንና መልሱን እንደሚያነብና ተከሣሹ በመልሱ ላይ የካደውን
ወይም ይክድ እንደሆነ እንደሚጠይቀው ይገልጻል :: የዚሁ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ ተከሣሹን ወይም ስለሱ ሆኖ የቀረበውን ሰው ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ጉዳዮች ወይም ሌሎች ነገሮች አብራርቶ ለማስረዳት ጠቃሚና ተገቢ መስሎ በገመተው ዘዴ የቃል ጥያቄ በማቅረብ ፍርድ ቤቱ ሊመረምራቸው እንደሚችል ይደነግጋል ፡፡ ከሣሽ ወይም ተከሣሹ እንዲብራራለት የሚፈልገው ጉዳይ ካለ በፍርድ ቤቱ በኩል እንዲጠየቅለት ማድረግ እንደሚችልም በዚሁ ድንጋጌ ላይ በግልጽ ሰፍራል ::
ይህ የሚያስገነዝበው የመስማት ሂደት የከሣሽና የተከሣሽ መገኘት የግድ የሚል ተሟጋቾቹም ጭምር የሚሣተፉበት ሂደት መሆኑን ነው :: ይህ ሂደት ፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮችንም ጭምር በማነጋገር ጉዳዩን ለዋናው የሙግት ደረጃ የሚያዘጋጅበት በመሆኑ የከሣሹና የተከሣሹ ( ወይም ወኪሎቻቸው ) መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡ ከሁለቱ የአንዱ አለመገኘት በሂደቱ መስተጓጎል የሚኖረው ተጽእኖም ከፍተኛ ነው :: በመሆኑም ከሌሎች ቀጠሮዎች ይበልጥ ባለጉዳዮች ጉዳዩ እንዲሰማ ቀጠሮ በተያዘበት ዕለት ባይቀርቡ የሚከተለው ውጤት ከሌላው የበለጠ ጠንካራ መሆኑ አስፈላጊ ነው :: በፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ ምዕራፍ 2 ( ከቁጥር 241-273 ) ያሉት ሁሉም ድንጋጌዎች የተሟጋቾች አለመገኘት ስለሚያስከትለው ውጤት ከመሰማት ሂደት ጋር አያይዘው የማያቀርቡትም በከፊል በዚህ ምክንያት ነው ::
ለማንኛወም የመሰማት ቀነ ቀጠሮ የተከሣሽ የጽሁፍ መልስ ለመቀበል ከሚሰጠው ቀነ ቀጠሮ የተለየ ነው :: በመሆኑም ክርክሩ በሚሰማበት ወቅት ተፈጻሚ እንዲሆኑ የተደነገጉትን ደንቦች የተለየ ባህርይና ዓላማ ባለው መልስ የመቀበል ቀነ ቀጠሮ ተፈጻሚ ማድረግ አግባብነት የለውም :: በፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥሮች 69፣70፣73 ያሉት ድንጋጌዎች ለመልስ በተቀጠረበት ቀን ተፈጻሚ ካልሆነ ከሣሹ ወይም ተከሣሹ ወይም ሁለቱም ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች የትኞቹ ናቸው የሚል ጥያቄ መነሣቱ የማይቀር ነው :: ከላይ እንደተገለፀው የፍትሀብሄር ሥነ ሥርዓት ሕጉን ቁጥር 67 ፣ 70፣73 እና ሌሎች ተዛማጅ ድንጋጌዎች ከተከራካሪዎች አንዱ ወይም ሁለቱም ጉዳዩ ለመሰማት ( hearing ) በተቀጠረበት ቀን ያልቀረቡ እንደሆነ ብቻ ተፈጻሚ ስለሚሆኑ ጉዳዩ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ከሣሽ ( እንደነገሩ ሁኔታ ይግባኝ ባይ ) ወይም ተከሣሹ የይግባኝ መልስ ሰጪ ) ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የሚሆን ሌላ የህግ ድጋፍ መኖር ይኖርበታል :: የፍትሀብሄር ሕግ ከ 192 እስከ 199 ባሉት ቁጥሮች ፍርድ ቤት እንዲፈፀሙ ያዘዛቸው ጉዳዮች ሳይፈፀሙ ሲቀር ስለሚሰጡ ትዕዛዞች የተለያዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል ፡፡ በቁጥር 199 ያለው ድንጋጌ አሁን ለያዝነው ጉዳይ በተለይ አግባብነት ያለው ነው :: የቁጥር 199 ( 1 ) “ ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም የቀረው ከተከራካሪዎቹ ወገኖች በአንደኛው ጉድለት የሆነ እንደሆነ መፈፀም ይገባው የነበረው ጉዳይ ያልተፈፀመ ቢሆንም እንኳ ፍርድ ቤቱ የጉዳዩን መፈፀም ሳይጠብቅ በዚያው ቀነ ቀጠሮ የመሰለውን ውሣኔ ለመስጠት ይችላል » በማለት ይደነግጋል ፡፡ የዚሁ ቁጥር ንዑስ ቁጥር ( 2 ) ደግሞ « ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም የቀረው በተከራካሪዎች ወገኖች ጉድለት ያልሆነ እንደሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ሌላ ቀጠሮ ይሰጣል » ይላል ::
መዝገብ የሚዘጋው አምርጦ አንድ ጉዳይ የተከሣሽን መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ከሣሽ ወይም ተከሣሽ ያልቀረቡ እንደሆነ ( እንደነገሩ ሁኔታ ይግባኝ ባይ ወይም መልስ ሰጪ ) ፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ መስጠት የሚገባቸው በዚህ ድንጋጌ መሠረት ነው :: ከድንጋጌው ንኡስ አንቀጽ አንድ ለማየት እንደሚቻለው ለቀጠሮ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም በቀረ ቁጥር መዝገብ የሚዘጋበት ሁኔታ እንደሌለ ግልጽ ነው ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ትዕዛዝ የሚሰጠው አንድ ጉዳይ እንዲፈጽም የታዘዘው ወገን ያን የታዘዘውን ጉዳይ ሳይፈጽም የቀረ እንደሆነ ነው :: በዚህም መሠረት መልሱን እንዲያቀርብ የታዘዘ ተከሣሽ ይህን ክንውን ሳይፈጽም ቢቀር ፍርድ ቤቱ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የመሰለውን ይወስናል ፡፡ ከሣሹ ለመልስ በተቀጠረበት ቀን ባይቀርብ ግን ከሣሹ እንዲፈጽመው የታዘዘው ነገር ስለሌለ ቀጣዩን ክንውን አስመልክቶ ትዕዛዝ ከመስጠት ውጪ የከሣሹን መዝገብ መዝጋት የሚያስችል አይደለም :: በመሆኑም የተከሣሽ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ያልቀረበ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የተከሣሹን የጽሁፍ መልስ ከማኀደሩ ጋር አያይዞ ጉዳዩ የሚሰማበት ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ለዚሁ አስፈላጊ ትዕዛዞችን መስጠት አለበት እንጂ መዝገቡን መዝጋት የለበትም :: ከላይ ተደጋግሞ እንደተገለፀው
ጉዳዩን ለመስማት ፍርድ ቤት ቀጠሮ በተያዘበት ቀነ ቀጠሮ ያልቀረበ እንደሆነ ነው ::
የተከራካሪዎች መቅረብን አስመልክቶ በሰፊው ማየት ያስፈለገን በያዝነው ጉዳይ ከፍተኛው ፍ / ቤት የይግባኝ ባይን መዝገብ የዘጋው መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ይግባኝ ባዩ አልቀረበም በማለት የፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ .73 ን በመጥቀሱ ነው፡፡ከመዝገቡ ለመረዳት እንደቻልነው የአሁኑ አመልካች ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የቀረው ጉዳዩን ለመስማት በተያዘ ቀጠሮ አይደለም ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ለመዝጋት ምክንያት አድርጎ የጠቀሰው የሕግ አንቀጽ የሰጠውን ትዕዛዝ ፈጽሞ የሚደግፍ አይደለም :: መልስ ለመቀበል በተያዘው ቀጠሮ ከይግባኝ ባይ የሚጠበቅ ክንውን ስላልነበረም ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን መልስ ተቀብሎ ቀጣዩን ቀጠሮ ( ክንውን ) በማስመልከት ትዕዛዝ ከሚሰጥ በስተቀር በተከሣሹ ላይ የፍ.ሥ.ሥሕቁ . 199 ን መሠረት በማድረግ የሚሰጠው ትዕዛዝ ሊኖር አይችልም :: በመሆኑም ከፍተኛው ፍ / ቤት የአመልካችን ይግባኝ የዘጋው እንዲፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሳይፈጽመው የቀረ ክንውን ሳይኖርና መዝገብ እንዲዘጋ ሕግ ያስቀመጠውን ሥርዓት ሳይከተል በመሆኑ ይህ ፍርድ ቤት አልተቀበለውም :: መዝገቡን መልሶ ላለመክፈት የሰጠው ምክንያት ባይሆንም ፍርድ ቤቱ ቀድሞውኑ መዝገቡን የዘጋው ሕጉ ያስቀመጠውን ሥርዓት ሳይከተል በመሆኑ ይህ ፍርድ ቤት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሠራውንና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማስተካከል ሲገባው ያለፈውን ግድፈት በሥ.ሥሕቁ .2 ዐ 7 እና 211 ( 2 ) መሠረት ማቃናት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል ፡፡
( 1 ) ከፍተኛው ፍ / ቤት በመቁ . ዐ 4 ዐዐዐ ጥር 21 ቀን 1995 የሰጠው ውሣኔ እንዲሁም
በመ.ቁ. የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል :: ( 2 ) ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ እንዲከፈት አድርጎ ካቆመበት
እንዲቀጥል ታዟል :: ( 3 ) ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ::

You must login to view the entire document.

Enter your email address and password to login.
Please enter a valid email address
Please enter your email address
Please enter your password
Password must be at least 8 characters long
Forgot your password?